ራስ ምታት የሚባለው ህመም በፊት በራስ ቅልና አንገት አካባቢ የሚከሰት የህመም ስሜት ሲሆን በጣም የተለመዱና በህብረተሰቡ ውስጥ በብዛት ከሚከሰቱ የህመም አይነቶች አንዱ ነው። በአማካይ በአንድ አመት ውስጥ ግማሽ ያክሉ በአዋቂ እድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን ያጠቃል። በአጠቃላይ ወደ 200 ሚያክል የራስ ምታት አይነቶች ያሉ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ለህይወት አስጊ ናቸው። አብዛኞቹ ግን ከሚያደርሱት ህመምና ስቃይ ውጪ ለህይወት አስጊ አይደሉም። ከእነዚህ ራስ ምታት አይነቶቹ ዓይነቶች ውስጥ በጣም የተለመዱትና በተደጋገሚ የሚከሰቱት ሁለት አይነት ራስ ምታቶች ናቸው። እነሱም ወጣሪ ራስ ምታት (Tension headache) ና ሚግሬን ራስ ምታት (Migraine headache) ናቸው።
ወጣሪ ራስ ምታት (Tension headache) – ይህ የራስ ምታት አይነት ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው በእራስ ቅል ዙሪያ ጠብቆ የታሰረ ጥምጣም የሚያስከትለውን አይነት ውጥረትና ህመም የሚያመጣ የራስ ምታት ነው።
ሚግሬን ራስ ምታት (Migraine headache) – ይሀኛው አይነት ራስ ምታት የራስ ቅልን አንድ ጐን ለይቶ የሚያም ሲሆን የህመሙ አይነትም ተደጋጋሚ የሆነ የመደብደብና በጦር ወይም በእንጨት የመወጋት አይነት ስሜት ነው። ህመሙ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች የቀን ተቀን ስራቸውን ለመተግበር ይቸገራሉ። መራመድ ወይም ደረጃ መውጣት ህመሙን ያባብሰዋል። ማቅለሽለሽና ማስታወክ እንዲሁም ድምፅ ወይም ብርሃን መፍራት ሊኖረው ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ላይ ሊጀምር ሲል በአይናቸው የተለያዩ ቀለማት ወይም ቀስተ ደመና ሊታያቸው ይችላል።
እራስ ምታት ሲነሳብኝ፣ እንዲሻለኝ ማድረግ የምችለው ነገር አለ ወይ?
አዎ የሚከተሉትን ነገሮች መሞከር ይችላሉ። ብዙ ሰዎችም በነዚህ እርምጃዎች ራስ ምታታቸው ይታገስላቸዋል።
ያለ ሀኪም ትዛዛዝ የሚገኙ የህመም ማስታገሻዎች፣ አንደ ፓራስታሞል፣ አይቡፕሮፌን፣ ዲክሎፌናክና ኢንደሜታሲን የመሳሰሉት መድሀኒቶች ከፋርማሲ ገዝቶ መውሰድ።
በቀዝቃዛ፣ ጨለም ያለና ፀጥታ የሰፈነበት ከፍል ውስጥ አረፍ ማለት። ይሄ በተለይ ለሚግሬን ራስ ምታት በጣም አስፈላጊ ነው።
የራስ ምታት ህክምና ምንድን ነው?
የራስ ምታት ህክምና 2 አላማ አለው፣ የመጀመሪያው አደገኛ አይነት ራስ ምታት እንዳልሆነ ማረጋገጥ። እነዚህ ራስ ምታቶች የጭንቅላት ደም መፍሰስ፣ ማጅራት ገትርና የመሳሰሉት ለህይወት አስጊ ራስ ምታቶችን መለየት መሰረታዊ የህክምናው አላማ ነው። ሁለተኛው አላማ ራስ ምታቱን መቆጣጠር ነው። ይህንን ለማድረግ ከላይ የተጠቀሱትን የማስታገሻ መድሀኒቶችና በሃኪም ብቻ የሚታዘዙ ሌሎች መድሀኒቶችን መጠቀም ያስፈልጋል።